የገበያ ኢኮኖሚ ዓይነት ጽንሰ ሐሳቦችን ማምታታት (ጌታቸው አስፋው)

ለመሆኑ የገበያ ኢኮኖሚ ምንድን ነው ስንት ዓይነት የገበያ ኢኮኖሚዎችስ አሉ፡፡

መንግሥት ጧት ማታ ኒዮ-ሊብራሊዝም እያለ የገበያ ኢኮኖሚን እያጥላላ መግለጫ ስለሚሰጥ ብዙ ሰው አንድ ዓይነት ብቻ የገበያ ኢኮኖሚ እንዳለና እርሱም ኒዮ-ሊብራሊዝም እንደሆነ ነው የሚገምተው፡፡

የልማት ኢኮኖሚ ነው ከሚለው ራሱ ከሚተዳደርበት የኢኮኖሚ መርህ ጋር የሚያነጻጽረውም የጭራቅ ያህል ስም የሰጠውን የኒዮ-ሊብራሊዝም የገበያ ኢኮኖሚን ነው፡፡

ኢኮኖሚስቶች የሚያውቁት ግን ኹለት ዓይነት የገበያ ኢኮኖሚዎች እንዳሉና ከእነዚህ የገበያ ኢኮኖሚ ዓይነቶች አንዱ በአዳም ስሚዝ የተተነተነው የገበያ ኢኮኖሚ ጽንሰ ሐሳብ፣ ከዐሥራ ስምንተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ እስከ ኹለተኛው የዓለም ጦርነት በምዕራብ አውሮፓና በአሜሪካ ይተገበር የነበረ፣ የሊብራል ነጻ ገበያ ኢኮኖሚ የገበያ ኢኮኖሚ የመጀመሪያ ምዕራፍ ነው፡፡

ኹለተኛው በኢኮኖሚስት ጆን ሜናርድ ኬንስ የተተነተነው፣ የግሉን ኢኮኖሚ በብሔራዊ ኢኮኖሚ ፖሊሲና በመንግሥት ቁጥጥር መምራት የሚለው ጽንሰ ሐሳብ፣ በሃያኛው ክፍለ ዘመን ከኹለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የተጀመረው የገበያ ኢኮኖሚ ኹለተኛ ምዕራፍ ነው፡፡

የሊብራል ነጻ ገበያ ኢኮኖሚ ገበያዎች በራሳቸው የፍላጎትና የአቅርቦት መስተጋብር ሕግጋቶች የገበያ ማጣሪያ ወይም የተመረተው ሁሉ የሚሸጥበት የተረጋጋ የሸቀጦች ዋጋ ፈጥረው የሚስተካከሉ ስለሆነ የመንግሥትን በፖሊሲም ሆነ በቁጥጥር ማስተካከያ ጣልቃ ገብነት አይሹም የሚል ነው፡፡

በኢትዮጵያ ገበያዎች ውስጥ በዓመት በዓል ወቅቶች ሽንኩርት ዶሮና በግ ቅቤ የመሳሰሉ የስጋና የወተት ዘሮች ዋጋዎች ሲወዥቁ እናያለን፡፡ ይህ የሚያመለክተው ገበያው ራሱን በራሱ ሊያስተካክል የገበያ ማጣሪያ የሸቀጥ ዋጋ ሊፈጥር አለመቻሉን ነው፡፡

ምክንያቱ ደግሞ ፍላጎት ከአቅርቦት መብለጡ ነው፡፡

ከዓመት በዓል ውጪም የሸቀጦች ዋጋ ተረጋግተው ገበያዎች የተስተካከሉ ወይም ያልተስተካከሉ፣ የሚወዥቁና የተወላገዱ መሆናቸውን ለመስተካከልና ላለመስተካከል፣ ለመዋዠቅና ለመወላገድም ምክንያታቸው ምን እንደሆነ አጥንተን ማረጋገጥ እንችላለን፡፡

በደርግ ሶሻሊስት ሥርዓተ ኢኮኖሚ ሁሉም ነገር ይወስን የነበረው በመንግሥት ነበር ብለን እንተወውና በዐፄ ኀይለ ሥላሴ ዘመን ዋጋዎች ይህን ያህል ያልተለዋወጡበት ምክንያት፣ ያኔ የነበሩትን የሸቀጦች ዋጋ ዛሬ ድረስ የምናስታውስበት ምክንያት፣ ገበያው ራሱን አረጋግቶ ዋጋዎችን ቋሚ ስላደረገ ነው ወይስ የመንግስት ገበያውን የመምራት ችሎታና ፖሊሲ ከዛሬው ተሽሎ ነው? ብለን ብንጠይቅ ኹለቱም መልስ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

በዚህ ዘመን ስለገጠመን የዋጋ ንረትና የዋጋ መዋዠቅ ለመረዳት ከራሳችን የሕይወት ተሞክሮ ተነስተን በገበያው ላይ የመንግሥት ቁጥጥር መኖር የለበትም፤ ቢኖርም እንኳ ጠበቅ ያለ ከሚሆን ላላ ቢል ይሻላል፤ ወይም መንግሥት በኢኮኖሚው ውስጥ እጁን ማስገባት የለበትም፤ የሚሉትን አማራጮች ለመወሰን፣ ገበያዎቻችንን አጥንቶ ማወቅ የትኛው ዓይነት ሸቀጥ በየትኛው የኢኮኖሚ ሥርዓት ውስጥ ይፈረጃል ብሎ መለየት ያስፈልጋል፡፡

በመሬት ግብይይት የመንግሥት ቁጥጥር የጠበቀ በመሆኑ የመሬት ገበያና የመሬት ዋጋ የተስተካከለ ነበር ወይስ የተወላገደ? በሠራተኛ ግብይይት የመንግሥት እጅ ስለሌለ የሠራተኛ ገበያና የሠራተኛ ዋጋ የተስተካከለ ነበር ወይስ የተወላገደ? በምግብ ምርቶች፣ በቤት ውስጥ ቁሳቁሶች፣ በአገር ውስጥ በሚመረቱ ሸቀጦች፣ ከውጭ በሚገቡ ሸቀጦች፣ በግንባታ ሸቀጦች፣ መንግሥት ገበያውን በሚቆጣጠርባቸውና በማይቆጣጠርባቸው ሸቀጦች፣ የአቅርቦት እጥረት ባለባቸውና በሌለባቸው ሸቀጦች፣ ብዙ ፈላጊ ባላቸውና በሌላቸው ሸቀጦች ምን ተገንዝበናል የሆነውስ ለምን ሆነ?

የሸቀጦች ዋጋዎች ተረጋግተው ፍላጎትና አቅርቦት እኩል ሆነው ገበያዎች ራሳቸውን በራሳቸው አስተካክለዋል ሲባል ዋጋዎች ለሁልጊዜ ቋሚ ይሆናሉ ማለት አይደለም፡፡

ፍላጎትና አቅርቦት እኩል ሆነው የተረጋጋ ዋጋ ፈጥረው ገበያው የተስተካከለ ይሆናል፡፡ የገበያ ማጣሪያ ዋጋም የተመረተውና ለገበያ የቀረበው ሁሉ እንዲሸጥ ያደርጋል ማለት፣ የሽንኩርትና የቲማቲም ገበያ በሰዓታት በቀናትና በሳምንታት ውስጥ ከአምስትና ስድስት ብር ወደ ሃያና ሰላሳአምስት ብር ከሃያና ሠላሳ አምስት ብር ወደ አምስትና ስድስት ብር የሚወዥቅበት ሁኔታ አይፈጠርም ማለት እንጂ፣ ከኢኮኖሚው ዕድገት ጋር፣ ከህዝቡ ገቢ መጠን ጋር፣ በዝግታ ዋጋዎች አይለዋወጡም ማለት አይደለም፡፡

ገበያው ተረጋግቶም በኢኮኖሚው ዕድገትና በሕዝቡ ገቢ መጨመር ምክንያት የአንዳንድ ዘመናዊ ሸቀጦች ዋጋ ሲጨምር የሌሎች ኋላቀር ሸቀጦች ዋጋዎች ይቀንሳል፡፡

ይህ ተመጣጣኝ የዋጋ ዕድገት በማንኛውም የገበያ አገር ውስጥ ይከሰታል ለእድገት አስፈላጊም ነው፡፡

ይህ የዋጋ ዕድገት ጤናማ ካልሆነው በአጭር ጊዜ ውስጥ አንድ ሲኒ ቡና ከሀምሳ ሳንቲም ተነስቶ አምስት ብር አንድ ኪሎ ቃሪያ ከሁለት ብር ተነስቶ ሐምሳ ብር ከሚገባበት የገበያ ዋጋ ሁኔታ የተለየ ነው፡፡

ገበያውን በልማት ኢኮኖሚ አስተዳደር ተክቼ የሊበራል ገበያን ከነጉድለቶቹ አስወግጄአለሁ እያለች ነጋ ጠባ በምትፎክር ኢትዮጵያ፣ ይህ ጤናማ ያልሆነ የዋጋ ንረት ሁኔታ የሚከሰትበት ምክንያት ምን እንደሆነ ጥናት የሚያስፈልገው ነው፡፡

በብሔራዊ ኢኮኖሚ ፖሊሲና በመንግሥት ቁጥጥር የገበያ ኢኮኖሚውን መምራት ሁለተኛው ምዕራፍ የገበያ ኢኮኖሚ አመለካከት ከኹለተኛው የዓለም ጦርነትና ታላቁ የኢኮኖሚ ቀውስ 1930ዎቹ ጀምሮ በምዕራብ አውሮፓና በአሜሪካ የሰፈነ የኢኮኖሚ ጽንሰ ሐሳብ ነበር፡፡

ሊብራሊዝም እንደገና በኒዮ-ሊብራሊዝም ስም ታድሶ በአሜሪካና አንዳንድ የአውሮፓ አገሮች እስከመጣበት እስከ 1980ዎቹ ድረስ በአሜሪካና በመላው ምዕራብ አውሮፓ ተተግብሯል፡፡

በብዙ የአውሮፓ አገሮች እስከ ዛሬም ድረስ አለ፡፡

የኹለቱን ታዋቂ ኢኮኖሚስቶች አመለካከት ልዩነት በምሳሌ መመልከት እንችላለን፡፡

በማንኛውም ምርምር መስክ የዝርዝርና የጥቅል ጥናቶችን አንድነትና ልዩነት ማወቅ ጠቃሚ ነው፡፡

ሰውን በዝርዝር ስንወስደው ስለ ልቡ፣ ኩላሊቱ፣ ሳምባው፣ ወዘተ ጤንነት በዝርዝር ምርመራ ማወቅ ይቻላል፡፡

በጥቅሉ በደም ምርመራም መታመም አለመታመሙ ይታወቃል፡፡

ጥያቄው ከዝርዝሩና ከጥቅሉ ምርመራ የቱ ይሻላል ነው፡፡

ልዩ ልዩ ገበያዎችን በሰውየው ዝርዝር አካላቶች ምሳሌ ብንወስድ፣ በአዳም ስሚዝ አመለካከት ሰውየው ጤናማ የሚሆነው እያንዳንዱ አካላቶቹ ጤናማ ሲሆኑ ነው በኬንስ ግን እያንዳንዱ አካላቶቹ ጤናማ የሚሆኑት መሉው ሰውነት ጤናማ ሆኖ የደም ዝውውሩ የተስተካከለ ሲሆን ነው፡፡ የደም ዝውውሩ ካልተስተካከለ ልቡም ኩላሊቱም ሳምባውም ይታመማሉ፡፡

ብሔራዊ ኢኮኖሚው በፖሊሲ ተመርቶ ካልተስተካከለ የሠራተኛ ገበያውም፣ የካፒታል ገበያውም የምርት ገበያውም ይዛባሉ፡፡

ከእነኚህ ኹለት የገበያ ኢኮኖሚ አመለካከቶች ውጪ ሌላ ሦስተኛ የገበያ ኢኮኖሚ ዓይነት አልተተነተነም፡፡

ከኹለቱ አንዱን ወይም ሁለቱንም የሚያዳብሩ ሐሳቦች በሊቃውንት ቢሰነዘሩም አገራት የሀብታሙን እና የድሀውን የኑሮ ደረጃ ለማቀራረብ ልዩ ልዩ የማኀበራዊ አገልግሎት ፕሮግራሞችን ቢነድፉም ከኹለቱ አመለካከቶች ማዕቀፍ ውጪ አይደሉም፡፡

የዚህ ዘመን ታላላቅ የኢኮኖሚ ሊቃውንት የሚመክሩትም ሁለቱም የሚደጋገፉ ባሕርያት ስላሏቸው አመጣጥኖ ማቀናበር ይሻላል የሚለውን ነው፡፡

የምዕራባውያን ካፒታሊስት አገሮች ኢኮኖሚ አመለካከቶችና ጽንሰ ሐሳቦች የእነኚህ ሁለት ጽንፎች ቅይጥ ጥምረት ወይም መሃል ቤት ነው፡፡

እንግሊዝና አሜሪካን የመሳሰሉ አገራት ወደ ሊብራል የገበያ ኢኮኖሚ ሲያጋድሉ ኖርዌይና ስዊድንን የመሳሰሉ የስካንዲኔቪያን አገራት ኢኮኖሚውን በብሔራዊ ኢኮኖሚ ፖሊሲ መምራትና በማኅበራዊ አገልግሎቶች ፕሮግራሞች የድሃውንና የሀብታሙን የኑሮ ደረጃ ማመጣጠንና ማቀራረብ ወደሚለው ያጋድላሉ፡፡

ኢሕአዴጎች ከእነዚህ ሁለት የገበያ ኢኮኖሚ ዓይነቶች አንዱን በብሔራዊ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ገበያውን መምራትን ደብቀው ራሳቸውን ከሊብራል ገበያ ጋር እያነጻጸሩ፣ የነርሱን ምድረ ገነት የሌላውን ሲኦል አስመስለው ነው የሚያወሩት፡፡ አጎንብሰው ተደብቀው ለመጓዝ ቢያስቡም የተጓዙትን ያህል ተጉዘው ይኸው አሁን መሽቶባቸው ገበያው ራሱ አጋለጣቸው፡፡

የደበቋቸው ሥራ አጥነት፣ የዋጋ ግሽበት፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት አደባባይ ወጥተው እየፎከሩባቸው ነው፡፡

የኢኮኖሚ ባለሙያ ስለ አገሩ ኢኮኖሚ አስተያየት የሚሰጠው በእነኚህ የኢኮኖሚ አመራርና አስተዳደር አመለካከቶች አቀያየጥ ካለው አቋሙ ተነስቶ ነው፡፡

እያንዳንዱ አገር የራሱ ተጨባጭ ሁኔታ ስላለው አንዱ የሌላውን ሊገለብጥ አይችልም፡፡

የሌላውን ለመገልበጥ መሞከርም ስህተት ላይ ይጥላል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *