ስለ ብጉር – ብጉር ምንድነው? እንዴትስ ማጥፋት ይቻላል?

ብጉር የቆዳ ችግር ሲሆን ዘይት (ቅባት) እና ቆዳ ላይ የሞቱ_ሴሎች የቆዳ ቀዳዳዎችን በሚደፍኑበት ጊዜ ይፈጠራል።

ትንንሽና ቀያይ ነጠብጣቦች በቆዳ ላይ በሚፈጠሩበት ጊዜ ብጉር በቆዳ ላይ እየታየ መሆኑ አመላካች ነው።

ከባድ ብጉር የሚባለው በመቶዎች የሚቆጠሩ ነጠብጣቦች (ጠቃጠቆ) በፊት፣ አንገት፣ ደረትና ጀርባ ላይ ሲከሰቱ ሲሆን እነዚህ ነጠብጣቦች ትልቅ፣ ደረቅና በጣም ህመም ያለው ቀይ እብጠት ሊሆኑም ይችላሉ።

ብጉር በወጣትነት (ጉርምስና) እድሜ ክልል ውስጥ ያሉትን በከፍተኛ ሁኔታ ያጠቃል። ከወጣትነት ዕድሜ በኋላ ግን ይጠፋል (ይቀንሳል)።

☞ ብጉር እንዴት ይከሰታል?

የተለያዩ የብጉር አይነቶች ቢኖሩም በጣም የተለመደው በወጣትነት ዕድሜ ላይ የሚከሰተው ነው። ወጣቶች ለአቅመ አዳም እና ሄዋን ሲደርሱ የሆርሞን መጠናቸው ይጨምራል።

ይህ የሆርሞን ለውጥ ደግሞ የቆዳን ዕጢ ብዙ ዘይት (ሴበም) እንዲያመርት ያደርገዋል። በቆዳ ቀዳዳ የሚወጣው ዘይት በዋናነት ቆዳ ጤናማ ወዝ እንዲኖረው ማድረግ ነው።

ብጉር የሚጀምረው ይህ ዘይት ከሞቱ የቆዳ ሴሎች ጋር ይቀላቀልና የቆዳን ቀዳዳ ይዘገዋል።

በዚህ ውህደት ውስጥ ባክቴሪያ ይገባና ያድጋል። ይህ ውህድ ከጎን ወዳለው የቆዳ ስጋ በማፈትለክ እብጠት፣ መቅላት እና መግል ይፈጥራል።

አንዳንድ መድሃኒቶች ለምሳሌ ኮርቲኮስቴሮይድ ወይም ሊቲየም ብጉሩ እንዲባባስ(እንዲያድግ) ያደርጉታል።

በብጉር የሚጠቁት ወጣቶች ብቻ ሳይሆኑ አንዳንድ ጊዜ ገና የተወለዱ ህፃናትም ብጉር ሊኖራቸው ይችላል።

ይህም የሚሆነው ህፃናቱ ከመወለዳቸው በፊት ከእናት ሆርሞን ወደ ህፃናቱ ስለሚተላለፍ ነው።

በብጉር የመጠቃት እድልን የሚጨምሩ ሁኔታዎች:

በብጉር መጠቃት የዘር ሀረግ ወይም ከቤተሰብ ጋር ይያያዛል። ወላጆች ከባድ ብጉር ካለባቸው ልጆች በብጉር የመያዝ እድላቸው ከፍተኛ ነው።

የወር አበባ በሚታይበት ዕድሜ ክልል ላይ የሚገኙ ሴቶች በብጉር የመጠቃት ዕድል አላቸው።

አብዛኛዎቹ ሴቶች የወር አበባ ከሚያዩበት ቀን በፊት ባሉት ቀኖች ላይ በጣም ትናንሽ የብጉር እባጮች ይኖራቸዋል።
.
ብጉርን የሚያባብሱ ሁኔታዎች፦

ቆዳን የሚፈገፍጉ (የሚፈትጉ) ነገሮች:

ለምሳሌ- ቀበቶ፣ ታይት፣ ሄልመንት፣ እጅ ላይ የሚታሰሩ ነገሮችና የመሳሰሉትን መጠቀም።

የፀጉርና ቆዳ መጠበቂያ ውጤቶች በተለይ በውስጣቸው የሚያሳክክ ንጥረ ነገር የያዙ ከሆነ።

ፊትን በተደጋጋሚ እየፈተጉ መታጠብ ወይም ፊትን በጣም እያሹ መታጠብ።

ሸካራ ሳሙና መጠቀም እና በጣም የሞቀ ውሃ መጠቀም።

ጭንቀትና ፊትን በተደጋጋሚ የመነካካት ልምድ መኖር።

ላብ ሲያልብ እና በፊት ላይ በዛ ያለ ፀጉር መኖር የፊት ቆዳ ዘይት እንዲኖረው ያደርጋል።

አንዳንድ መድሃኒቶች መውሰድ (ኮርቲኮስቴሮይድ፣ ባርቢቱሬትስ ወይም ሊትየም)

በዘይት እና ኬሚካል ማምረቻዎች አካባቢ መስራት፤

አትሌቶችና ሰውነታቸውን የሚገነቡ ስፓርተኞች ስቴሮይድ ስለሚወስዱ በብጉር የመጠቃት ዕድል አላቸው።

የብጉር መከላከያ መንገዶች:

ብጉርን በዘላቂነት መከላከል ባይቻልም እንዳይባባስ የሚወሰድ እርምጃዎችና ጥንቃቄዎች ግን አሉ። ከነዚህም መካከል፦

በዝግታ ወይም በጣም ሳያሹ መታጠብ ለቆዳዎ ጤንነት አስፈላጊ ነው። በጣም ማሸት፣ መጥረግ፣ መፈተግ ወይም መፈግፈግ ተገቢ አይደለም።

በጣም እንዳያልብዎ መጠንቀቅ። ላብ እንዲያልበን የሚያደርጉ እንቅስቃሴዎች ካደረግን በኋላ ወዲያው መታጠብ።

ፀጉርዎ ቅባት ካለው ወይም ከበዛበት መታጠብ፤

•ጭንቀትን አለማብዛት፤
• አንዳንድ የፀጉር መንከባከቢያ ምርቶችን መጠቀም ማቆም።
ለምሳሌ፦ ጄል፣ ክሬምና የመሳሰሉት…..
• ፊትዎን ቶሎ ቶሎ ከመንካት መቆጠብ
• ለስላሳ የኮተን ልብሶችን መጠቀም። በተለይ ከቆዳ ጋር ንክኪ ያላቸው ከሆነ…
• ከቅባት እና ኬሚካል ጋር ያለዎትን ግንኙነት መቀነስ ለምሳሌ እንደ ፔትሮሊየም የመሳሰሉ……

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *