ሁለት ጄኔራሎች ስራቸውን በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቃቸው አነጋጋሪ ሆኗል

ሁለት ጄኔራሎች ስራቸውን በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቃቸው አነጋጋሪ ሆኗል

የህወሃት መራሹ ቡድን ጥቅም በማስከበር ሲሰሩ የቆዩ ሁለት ጄኔራሎች ሲቪል በመሆን ግልጋሎት ከሚሰጡባቸው ተቋማት ሐላፊነታቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ለቀቁ የሚለው ዜና አነጋጋሪ እንደሆነ ነው።

ጄኔራሎቹ በወታደራዊ ማእረግ ሳይሆን በሲቪሊነት ከሚመሯቸው «ሜቴክና ኢንሳ» ስራቸውን በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቃቸው ቢነገርም ከመከላከያ ሰራዊቱ እራሳቸውን አለማግለላቸው ታዉቋል።

ሜቴክ በመባል የሚታወቀውን የህወሃት ጄኔራሎች የሚቆጣጠሩትን ኩባንያ ሲመሩ የነበሩት ብርጋዴል ጀነራል ክንፈ ዳኘው ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆኑ የመንግስት ፕሮጀክቶችን ኦዲት ሳያስደርጉ፣በስኳርና በማዳበሪያ ፋብሪካዎች ዉስጥ የነበረው ዝርፊያ ሳይመረመር፣በመንገድ ትራንስፖርትና በአባይ የህዳሴ ግድብ የሙስና መረብ ዉስጥ የነበራቸው ሚና በተገቢው መልኩ ሳይጠናና በብድር የተጀመሩ የሜቴክ ፕሮጀክቶች የደረሱበት ደረጃ ሳይታወቅ የሜቴክ ሐላፊነታቸውን በፍቃዳቸው ለመልቀቅ መሞከራቸው የህወሃት መራሹ አገዛዝ መሻገት አመላካች ነው የሚል ክስ እየቀረበበት ነው።

በሌላ በተያያ ዜና የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) ዳይሬክተር የሆኑት ሜጄር ጄኔራል ተክለ-ብርሃን ወልደ-አረጋይ ስራቸውን በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቃቸው የሚያመላክት መረጃ ለህወሃት መራሹ አገዛዝ ቅርበት ያላቸው አካላት እያሰራጩ ነው።

ጄኔራሉ ቀደም ሲል በስለላ፣በጠልፋና በአፈና መዋቅር ዉስጥ ያሁኑ ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ በምክትልነት አብረዋቸው ይሰሩ እንደነበር ይታወቃል።

ሜጄር ጄኔራል ተክለ-ብርሃን ወልደ-አረጋይ ቀደም ሲል በርሳቸው ሐላፊነት ስር የነበሩት ዶ/ር አብይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስቴር በመሆናቸውና በርሳቸው ላለመታዘዝ ሆን ብለው ስራቸውን መተዋቸውን የሚጠቅሱ መረጃዎች ቢወጡም የተረጋገጠ ነገር የለም።

ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ተንታኞች በህወሃት አንጃዎች መካከል ያለ የስልጣን ሽኩቻ ዉጤት ሊሆን ይችላል በማለት አስተያየት እየሰጡበት ነው።

ሁለቱ ጅነራሎች ስራቸውን በገዛ ፍቃዳቸው ስለ መልቀቃቸው የሚያስረዳ መረጃ በህወሃት መራሹ መንግስት በኩል ለግዜው ይፋ አልሆነም።

ለስርዓቱ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ይህንን ዜና ማሰራጨታቸው በህዝብ ዘንድ ብዥታን ለመፍጠር የሚደረግ ጥረት ሊሆን ስለሚችል ጥንቃቄ መደረግ እንዳለብት የሚጠቅሱ ብዙ ናቸው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *