ለአስም ህመምተኞች ጠቃሚና ጎጂ ምግቦች

ለአስም ህመምተኞች ጠቃሚና ጎጂ ምግቦች

ባለፉት ጊዜያት ለስኳር ህመምተኞች እና በኩላሊት ለሚሰቃዩ ጠቃሚ የሆኑ የአመጋገብ ጥቆማዎችን አድርገናል፡፡

እነሆ የአስም ህመምተኞች ተራችሁ ደርሷልና ከአመጋገብ አኳያ ምን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባችሁ 10 ጥቆማዎችን ይዘንላችሁ መጥተናል፡፡

ነገ በኔ ነው እና የበሽታው ተጠቂ ያልሆናችሁ ተከታዮቻችን ሼር በማድረግ ለተቸገሩ ሰዎች እንዲያነብቡት እንርዳቸው፡፡

ለአስም ህመምተኞች የሚሆኑ እና የማይሆኑ ተብለው የተለዩ ምግቦች የሚከተሉት ናቸው፡፡

1. ነጭ ሽንኩርት

ለበርካታ ዘመናት የፈዋሽ ምግቦችን ዝርዝር በቁንጮነት ሲመራ ኖሯል፡፡ አሁንም ተወዳዳሪ አልባ መሆኑን የተለያዩ ጥናቶች እየመሰከሩለት ነው፡፡

ለአስም ፈዋሽ እንደሆነም ዶ/ር ግርሃም ይመሰክራሉ፡፡ እ.ኤ.አ በ2009 የተካሄደ አንድ ጥናት ግን ካንሰር አማጪ ፍሪ ራዲካልሶችን የሚያጠፋው allicin የተሰኘ ንጥረ ነገር በነጭ ሽንኩርት እንደይገኝ ገልጾ ነበር፡፡

2. አፕል

በእንግሊዝ የተካሄደ አንድ ጥናት በሳምንት ከ2 እስከ 5 አፕል የሚመገቡ ሰዎች አስማቸው የመቀስቀሱ መጠን በ32% ዝቅ ብሎ መገኘቱን ገልጧል፡፡

በፍሬው ውስጥ የሚገኘው Flovonoids የተሰኘው ንጥረ ነገር ለዚህ ውጤት መገኘት አስተዋፅኦ ሳይኖረው እንደማይቀርም ተገምቷል፡፡

3. ካሮት

በሰውነት ወደ ቫይታሚን ኤ የሚቀየረውን ቤታካሮቲን የተሰኘ አንቲኦክሲደንት በካሮት ውስጥ በብዛት ይገኛል፡፡

በቤታካሮቲን ላይ እየተካሄዱ ያሉ ቅድመ ጥናቶች ንጥረ ነገሩ በእንቅስቃሴ የሚነሳ አስምን ለመቆጣጠር ያስችላል፡፡ ካሮት ለአይን ጤንነት እና ለበሽታ መከላከል አቅም ከሚሰጠው ጥቅም በተጨማሪ ከልብ፣ ከካንሰርና ከመርሳት (አልዛይመር) በሽታዎች ይጠብቃል፡፡

ቤታካሮቲን በስኳር ድንች እና በቃርያ ውስጥም ይገኛል፡፡

4. እንቁላል

በአንዳንድ ሰዎች ላይ ሽፍታ በመፍጠር እንቁላል አለርጂ ለመቀስቀስ ምክንያት ነው፡፡

አስም ሊነሳ ሊያደርግም ይችላል፡፡ የእንቁላል አለርጂ በተለይ በህፃናት ላይ የሚታይ ሲሆን እያደጉ ሲሄዱ ብዙዎችን ይተዋቸዋል፡፡

ልጅዎ የእንቁላል አለርጂ ካለበት(በሃኪም ተመርምሮ መታወቅ ይገባዋል) እንቁላልና በእንቁላል የተሰሩ ምግቦችን እንዳይመገብ ያድርጉ፡፡

ብናኝ በሚበዛባቸው፣ እምክ እምክ በሚሸቱ ቢሮዎችና ቤቶች የሚሰሩና የሚኖሩ ሰዎች የአስም ስሜት እንዳይዳብርባቸው ሲባል እንቁላልን አዘውትረው እንዲመገቡ አይመከርም፡፡

5. ተልባ

ተልባ በኦሜጋ-3 አሲዶችና በማግኒዥየም የበለጸገ ነው፡፡ አንዳንድ ጥናቶች በዓሳ ውስጥም በከፍተኛ መጠን የሚገኘው ኦሜጋ-3 ለአስም ጥሩ ነው ለማለት የሚያስችል ቀዳሚ ውጤት እንዳገኙ ይገልፃሉ፡፡

6. ቡና

በየጊዜው ቡናን የተመለከቱ መረጃዎች ይወጣሉ፡፡ ይጠቅማል ይጎዳል የሚሉ፡፡

አስምን በተመለከተ ግን ቡና ጥቅሙ ያመዝናል፡፡

በቡና ላይ የተደረጉ ሰባት ጥናቶችን የመረመረ አንድ የሳይንቲስቶች ቡድን ቡና ከተጠጣ በኋላ ባሉ አራት ሰዓታት የአየር ቧንቧዎች በተሻለ ሁኔታ እንዲሰሩ እንደሚያደርግ ደርሼበታለሁ ብሏል፡፡

ኒዮርክ በሚገኘው የሌኖክስ ሂል ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ሮበርት ግራሃም ‹‹ካፌይን አየር መተላለፍን ያሻሽላል፡፡

ጥቁር ሻይም ጠቃሚ ነው፡፡››

ሲሉ የቡና አስተዋፅኦ የማይናቅ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡

7. ወተት

አንዳንድ መረጃዎች ወተትና ውጤቶቹ አስምን እንደሚቀሰቅሱ ይገልፃሉ፡፡

ጥቂት ሰዎች ደግሞ የወተት አለርጂ አለባቸው፡፡ ይህ አለርጂ ለመተንፈስ መቸገር፣ ሳል እና ሌሎች የመተንፈሻ አካል ችግሮችን ይፈጥራል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ወተት የቫታሚን ዲ ምርጥ መገኛ በመሆኑ የአስም ምልክቶችን ለማለዘብ ይረዳል፡፡

ኤክስፐርቶች አስምን ለመቆጣጠር ዋናው መላ አለርጂ ቀስቃሾችን በይፋ ማወቁ ላይ ነው ይላሉ፡፡

8. ኦቾሎኒ

በአንዳንድ ሰዎች ላይ አደገኛ አለርጂ ይቀሰቅሳል፡፡

በሌሎች ላይ ደግሞ የአስም አለርጂ ይፈጥራል፡፡

አንድ ጥናት የኦቾሎኒ አለርጂ ያለባቸው ሕፃናት ከሌሎች በተለየ በአስም የመጠቃ እድላቸው ከፍተኛ መሆኑ ተገልጧል፡፡

በርካታ አስም ያለባቸው ለኦቾሎኒ አለርጂ የሆኑ ህፃናት በሳር፣ በአረም፣ በድመቶች፣ በአቧራ፣ በአበባ ብናኝ እና በመሳሰሉት አስማቸው ሊቀሰቅስ ይችላል፡፡

ብዙዎቹም ሆስፒታል በመተኛት ህክምና ለመከታተል ይገደዳሉ፡፡

9. ጨው

አየር መተላለፊያ ትቦዎችን ያጠባል፣ በሰውነት ውስጥ የውሃ እጥረት እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡ ‹‹የአስም ምልክቶች የሚታያቸው ሰዎች ዝቅተኛ ጨው መመገብ ይኖርባቸዋል›› ይላሉ ዶ/ር ግራሃም፡፡

10. ወይን

በርካታ ጥናቶች በውስጡ የሚገኘው sulfites የተሰኘ ንጥረ ነገር አስም እንዲቀሰቀስ እንደሚያደርግ ፅፈዋል፡፡ ሌሎች ጥናቶችም ራሱ አልኮሉ ወይም ሌላ ግብአት የፈጠረው ሊሆን ይችላል ቢሉም ወይን አስምን ይቀሰቅሳል በሚለው ላይ ግን ተስማምተዋል፡፡

 

ምንጭ፡- አዲስ ጉዳይ መፅሄት

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *