በመዲናዋ የኩላሊት ህክምናን በአንድ ቦታ የሚሰጥ ማዕከል ሊቋቋም ነው

በአዲስ አበባ ሁሉንም የኩላሊት ህክምናዎች በአንድ ቦታ ለመስጠት የሚያስችል ማዕከል ሊያቋቁም መሆኑን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ።

 

በመላው ዓለም ግማሽ ቢሊዮን ህዝብ ጽኑ የኩላሊት ህመምተኞች ሲሆኑ፥ ከዚህ ውስጥ 78 በመቶ ያህሉ በታዳጊ አገራት እንደሚገኙ የዓለም የጤና ድርጅት ከአንድ ዓመት በፊት ያወጣው መረጃ ያስረዳል።

 

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የኩላሊት ህመም ከ15 ዓመት በፊት ከነበረበት 25ኛ ደረጃ ገዳይ በሽታነት ባሳለፍነው የፈረንጆች ዓመት 15ኛው ገዳይ ህመም ሆኗል።

 

በኢትዮጵያ በየዓመቱ የኩላሊት ህክምና የሚያስፈልጋቸው ህሙማን ቁጥር 60 ሺህ መድረሱን የጤና ጥበቃ ሚኒሰቴር መረጃ ያመለክታል።

 

በሚኒስቴሩ የክሊኒካል አገልግሎት ተወካይ ዳይሬክተር ዶክተር ይበልጣል መኮንን እንደገለጹት፥ ህክምና የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ቁጥር ከዓመት ዓመት እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል።

 

በዚህም ህክምናውን ለሚፈልጉ ዜጎች የተሟላ የኩላሊት ህክምናዎችን ያካተተ ማዕከል ለማቋቋም የሰው ሀይል የማደራጀት፣ በጀት የማዘጋጀትና ሌሎች የዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ ነው።

 

በ14 ሚሊየን ዶላር ወጪ የሚገነባው ይህ ማዕከል በኢትዮጵያ እና በኳታር መንግስት ድጋፍ በአዲስ አበባ ሚኒሊክ ሆስፒታል ግቢ ውስጥ እንዲቋቋም መወሰኑን ዶክተር ይበልጣል ገልጸዋል።

 

ማዕከሉ የኩላሊት እጥበት፣ ንቅለ ተከላ፣ የኩላሊት ህክምና ማሰልጠኛ እና ሌሎች አገልግሎቶችን ያካተተ እንደሚሆንም አብራርተዋል።

 

በተጨማሪም 50 የኩላሊት እጥበት ህክምና መስጫ ማዕከላትን በዩንቨርሲቲ ሆስፒታሎች እና በሌሎች ተቋማት በማቋቋም በሁሉም ክልሎች ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑን አክለዋል።

 

በኬሚካሎች እና በምግብ መመረዝ ምክንያት ለሚፈጠሩ ህመሞች ህክምና የሚሰጡ ማዕከላትንም በክልሎች ለማስፋፋት መታቀዱን ጠቅሰዋል።

 

የደም ግፊት፣ የስኳር ህመም፣ መመረዝና ኢንፌክሽኖች ለጽኑ የኩላሊት ህመም መንስኤዎች ሲሆኑ፥ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ አትክልቶችን እና ፍራፍሬዎችን መመገብ፣ አልኮል እና ሌሎች እፆችን አለመውሰድ ከህመሙ መከላከያ መንገዶች መካከል ይጠቀሳሉ።

 

ምንጭ፦ ኢዜአ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *