የገነባነውን እንዴት መጠገን አቃተን?

 የበኩር ገዜጣ ርዕሰ አንቀጽ ነው፡፡
ያንብቡት! ባህርዳር ፡ህዳር 26/2010 ዓ/ም(አብመድ) “ወደ አፍሪካ ከሄዳችሁ ኢትዮጵያን የመጀመሪያ፤ ምርጫችሁ አድርጉ፤ ወደ ኢትዮጵያ ከሄዳችሁ ደግሞ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን መጐብኘትን ያሥቀድሙ” የሚለው የተለመደ የውጭ ሀገር ጐብኝዎች አባባል ያለምክንያት የተጠቀሠ አይደለም::

ኢትዮጵያን ከሚያሳውቋት ቅርሶቿ መካከል የመጀመሪያውን ቦታ የሚይዙት የላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናት በመሆናቸው ነው::
“ወደ ኢትዮጵያ ሄደህ ነበር?” “አዎ” “ላሊበላን ጐበኘህ?” “አልጐበኘሁም!” “እንግደያውስ ወደ ኢትዮጵያ እንዳልሄድክ ቁጠረው” የሚሉ ንግግሮችም በውጭ ሀገር ጐብኝዎች ዘንድ የተለመዱ ናቸው::

ይህ የሆነበት ዋናው ምክንያት ደግሞ ኢትዮጵያን ያለላሊበላ ለማሰብ ሥልሚከብድ ነው::
የኢትዮጵያ የመጀመሪያው መታወቂያም የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ናቸውና አባባሉ ብዙም የተጋነነ አይሆንም::

ከ900 ዓመታት በፊት የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርሲያናትን አፄ ላሊበላ አነፅዋቸው:: እጅግ አሥገራሚ ከመሆናቸውም ባሻገር እስከ ዛሬ ድረስ ምስጢራቸው በዘመናዊው ዓለም ሊደረስባቸው ያልቻሉ የኪነ ህንፃ ጥበብ ናቸው ፣በዚህም የዓለምን ህዝብ ማስደመማቸውን ቀጥለዋል::

እነዚህ ድንቅ ቅርሶች ኢትዮጵያዊያንን እያኮሩና የጥንታዊ ሥልጣኔ ባለቤትነታችንን እያሥመሠከሩ ዘመናትን ተሻግረው አብረውን አሉ::

የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እጅግ የረቀቀና ዘመናትን ተሻግሮ ሊደረስበት ያልቻለ የኪነ ህንፃ ምስጢር የያዙ በመሆናቸው ብዙ የውጭ ዓይኖችም ይበዘባቸዋል ታሪክን ለመሻማትና ታሪክን ለመዝረፍ በየጊዜው የሚመጡት መላምቶችና የሀሠት ትንተናዎችም ይሄንን የሚያሳዩ ናቸው::

ጥንታዊ አባቶች በረቂቁ የማስተዋል ጥበብ ታግዘው… በልዩ የመመሰጥ ብቃታቸው ያነጿቸውን የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ወደራስ ለማሥጠጋት የሚደረገው ሩጫ ዘመናትን ያሥቆጠረ ጉዳይ ነው::

 

የገነባነውን እንዴት መጠገን አቃተን?

 

ዳሩ ኢትዮጵያውያን የታሪክ ተመራማሪዎች ይህንን የተዛባ እና አሳማኝ ምክንያት የሌለው የታሪክ ንጥቂያ በአሳማኝ የታሪክ ማስረጃ እያቀዘቀዙት ቢገኙም ቅሉ::

ከዚህ ባልተናነሰ አንዳንድ የውጭ ሀገር ምሁራንም ለህሊናቸው ቆመው ላሊበላ የኢትዮጵያውያን ድንቅ የሥልጣኔ አሻራና የኪነ ህንፃ ውጤታቸው መሆኑን እያረጋገጡ በመምጣታቸው የአንድ ሰሞን ፍትጊያውን ቀዝቀዝ ያደረገው ይመሥላል::

ከእነዚህ መካከል ደግሞ አሜሪካዊቷ ድሩሲላ ዱንጂ ሒውስተን ተጠቃሽ ናት::
ኢትዮጵያውያን ምን ያህል ተዓምር መሥራት እንደሚችሉ “ፒራሚድ ገንቢዎቹ ጥንታዊ ኢትዮጵያዊያን!” በሚለው መፅሐፏ ቁልጭ አድርጋ አሥቀምጣዋለች::

ይሁንና ከ900 ዓመታት በፊት ድንቅ የኢትዮጵያ ልጆች የገነቧቸው የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የመፈራረስ አደጋ ተጋርጦባቸው ረጅም ዓመታትን በሥጋት ውስጥ ይገኛሉ::
በዚህ ዝናቡና ፅሐዩ ሲፈራረቅባቸው በዚያ ደግሞ ሰው ሠራሹ ጉዳት ህልውናቸውን እየተፈታተነው ይገኛል::
የተሠራው መጠለያም ይበልጥ ችግራቸውን እያወሳሰበው ይገኛልና የላሊበላ ነዎሪዎች የድረሱልን ጥሪ ለኢትዮጵያ ህዝብ ሲያሰሙ ቆይተዋል::

መጠለያው ወይ በነፋስ ወደላይ ተነሥቶ አብያተ ክርስቲያናቱ ላይ የመውደቅ ወይም ወደታች ተደርምሶ የማፍረስ ሥጋት ሥለደቀነባቸው፣ “እንቅልፍ የለንም” ሲሉ ለወገኖቻቸው ድረሱልን ሲሉ እየጮኹ ይገኛሉ::
ይህንን ጩኸት ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ መቀመጥ ደግሞ ከታሪክ ታወቃሽነት ሊያድነን አይችልም::
የሚገርመው እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት ለረጅም ዓመታት ለጉዳት ተዳርገው ለመጠገን አለመቻላችንም እቆቅልሹ ያልተፈታ ጉዳይ መሆኑ ነው::

ከ1930 ጀምሮ ጥገና የተደረገላቸው በውጭ ሀገር ዜጐች መሆኑ ደግሞ እንቆቅልሹን የበለጠ ያወሳስበዋል::
የገነባነውን እንዴት መጠገን አቃተን?፤ የዘመን እንቆቅልሻችንንስ እንዴት መፍታት ተሳነን?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *