ቡና የመጠጣት ልምድ እድሜን ሊያረዝም ይችላል

ቡና የመጠጣት ልምድ እድሜን ሊያረዝም ይችላል-ጥናት በቀን ከሶስት እስከ አራት ስኒ ቡና መጠጣት ደህንነት እንዲሰማን ከማድረግ ባሻገር ከልብ በሽታ የሚታደግና ረዥም እድሜ ለመኖር እንደሚያስችል ጥናት ጠቆመ፡፡

ዩፒአይ ይዞት በወጣው ዘገባ የጥናቱ ውጤት ላይ የተደረሰው በመካከለኛ ደረጃ ቡና የሚጠጡ ሰዎችን መሰረት አድርገው ቀደም ብለው የተካሄዱ 200 ጥናቶችን ደግሞ በመተንተን ነው፡፡

አዲስ በተደረገው የጥናቱ ትንተና በመካከለኛ ደረጃ ቡና የሚጠጡ ሰዎች ለፕሮቴስት፣
ለማህፀንና የሽንት ቧንቧ፣የቆዳ እና የጉበት ካንሰር፣ለሁለተኛ አይነት የስኳር ህመምና ፣
የጉበት በሽታ፣የሃሞት ጠጠር፣ለሪህ እና ለመርሳት በሽታ የመጋለጣቸው መጠን ይቀንሳል፡፡

በፓርኪንሰን፣በድብርትናበአልዛይመር የመጠቃት እድልን እንደሚቀንስም ጥናቱ ጠቁሟል፡፡

ነገር ግን ነብሰ ጡር ሴቶች የፅንሱን ያለጊዜ መወለድና ውስብስብ ችግሮች ስለሚያስከትል ቡናን አብዝተው መጠቀም እንደሌለባቸው ጥናቱ ጠቁሟል፡፡

የጥናቱ መሪ ከሳውዝ ሃምብተን ዩኒቨርሲቲ የህብረተሰብ ጤና ስፔሻሊስት ዶክተር ሮቢን ፑልና ከስኮትላንድ ኤድንበርግ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ጋር በጥምረት ባካሄዱት ጥናት ቡናን በመካከለኛ ሁኔታ የሚጠጡ ሰዎች ምንም ከማይጠጡት ይልቅ በማንኛውም በሽታ ቀድሞ የመሞት እድላቸው የቀነሰ ነው ብለዋል፡፡

ቡና በቀን እስከ ሶስት ስኒ ሲወሰድ ጠቃሚው ነገር የሚገኝ ሲሆን በዝቶ ሲወሰድም የጎላ የጤና ጠቀሜታ የለውም ፡፡

የጥናቱ ግኝት የቡና ወዳጆችን የሚያስደስት እንደሆነ የተናገሩት በኒውዮርክ ከተማ ሊኖክስ ሂል ሆስፒታል የሴቶች የልብ ጤንነት ዳይሬክተር ዶክተር ሱዛን ስቴንባም

“ብዙ ሰዎች ቡና አለመጠጣት ጤናማ ህይወትን መምራት እንደሆነ ቢያስቡም ጥናቶች የሚያመለክቱት ግን ይህ ሁልጊዜ ትክክል እንዳልሆነ ነው ብለዋል፡፡

”በቀን እስከ ሶስት ስኒ ቡና መጠጣት ጤናማ ህይወት የመኖር አንዱ መገለጫ ነው፤የልብ ህመምን መቀነስ ብቻ ሳይሆን እንደ አልዛይመርና ፓርኪንሰን ያሉ የነርቭ ህመሞችን ተጋላጭነት ይቀንሳል፡፡

በተለይም ጠዋት የምንጠጣው ቡና የተረጋጋ አእምሮ እንዲኖረን ያስችላል ብለዋል ዶክተር ስቴንባም፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *